በስፔን – ቫሌንሽያ ሲካሄድ በሰነበተው 23ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ተካፍሎ ከተዘጋጀው 4 የወርቅ ሜዳልያ 3ቱን በማግኘት ከዓለምም ከአፍሪካም አንደኛ በመሆን ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልኡካን ቡድን በዛሬው እለት መጋቢት 18/2010 ዓ. ም ከማለዳው 1፡30 ሰዓት ጀምሮ በተካሄደ የእንኳን ደህና መጣችሁ ሥነ ስርዓትና የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት አሰጣጥ ተደርጎለታል፡፡

በዚህ ወቅት የኢፌዲሪ ወ/ስ/ሚኒስቴር ሚኒስትር ተወካይ አቶ መንግስቱ ሳህሌ ባሰሙት ንግግር ሚ/ር/መ/ቤቱ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽነው ጎን በመሆን ድጋፉን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በበኩሉ ባስተላለፈው የእንኳን ደህና መጣችሁና እንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ‹‹ድላችሁ የሃገራችሁን ህዝብ አኩርቷል፡፡ ይሁንና ዛሬ የበለጥናቸው ሌሎች ሃገራትም ዝም ብለው የማይመጡ በመሆኑ አሁንም ጥረታችንን አጠናክረን እንደገና በዓለም አደባባይ የሃገራችንን ስምና ሰንደቅ ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠብቀን ማወቅ ያስፈልጋል፤›› በማለት ገልጧል፡፡

ክቡር ፕሬዝዳንቱና ክብርት ኮሎኔል፣ ሎሬት፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የኢትየዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትና የኢት/ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማቱን በየተራ ሰጥተዋል፡፡

ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ቀጥሎ ክቡር ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የእንኳን ደህና መጣችሁና የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ እነዚህን በድል ወደ ሃገራቸው የተመለሱ አትሌቶች በገንዘብ ሽልማት ለማበረታታት መዘጋጀቱንና ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ጋር ሂደቱን በቀጣይ እንደሚያከናውን አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም በግለሰቦች ቃል የተገባው የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት አሰጣጥ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኃላፊ በአቶ ቢልልኝ መቆያ አመካይነት ተከናውኗል፡፡ በዚህ ወቅት አቶ ቢልልኝ እንደገለጹት ቃል የተገቡት ሽልማቶች በክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴና በአቶ በላይነህ ክንዴ እንደነበር አስታውሰው በውድድሩ ሪከርድ በመሰበሩ ሽልማቱም ቃል ከተገባው በእጥፍ ማደጉን ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከማለዳው 2፡45 ሰዓት ላይ በቡድን የፎቶግራፍ ሥነ ስርዓት ተጠናቋል፡፡

ስለሺ ብሥራት –  በኢአፌ የኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ኤክስፐርት፤

Similar Posts
Latest Posts from