የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ5ኛ ጊዜ በአልጀሪያ ክሌፍ ከተማ መጋቢት 8/2010 ዓ. ም. በተካሄደው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ለተካፈለውና በድል ለተመለሰው የልኡካን ቡድናችን ወደ 240,000 ብር የሚጠጋ የማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷል፡፡

በሽልማት ስነ ስርአቱ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ ባስተላለፈው መልእክት ከእስከ አሁኖቹ ውጤቶቻችን የተሻለ ቢሆንም መኩራራት እንደማይገባና በሥነ ምግባር የታነጸና በስልጠና የታገዘ ጠንካራ ቡድን በመገንባት የሃገራችንን ውጤታማነት በብልጫ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ የቡድኑ መሪ አቶ አድማሱ ሳጂ በበኩላቸው በተዘጋጁት ልክ ውጤት አለመምጣቱን ገልጸው ለዚህ ምክንያቱ አብዛኛዎቹ አትሌቶች ጾመኛ በመሆናቸው እንደነበር ተናግረዋል፤ አያይዘውም በአልጀሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላደረገላቸው መልካም አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከፌዴሬሽኑ ሽልማት በኋላ ለቡድኑ በሽኝቱ ወቅት ሽልማት ለማበርከት ቃል ገብተው የነበሩ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ እና እቡር አቶ በላይነህ ክንዴም ሜዳልያ ላስመዘገቡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ሰጥተዋል፡፡ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ከቡድኑ ጋር በመጓዝ በስልጠናውና በውጤቱ ላይ ከፍ ያለ ሚና ለነበራቸው አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱም የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡

በተያያዘ ዜናም በ23ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ላይ ኢትዮጵያን የሚወክለውና በወንዶችም በሴቶችም 15 አባላትን የያዘው የልኡካን ቡድን ሰኞ መጋቢት 11/2010 ዓ. ም ለሊት ላይ ወደ ስፍራው ስፔን ቫሌንሽያ አቅንቷል፡፡

በስለሺ ብሥራት – የኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ፤

Similar Posts
Latest Posts from