የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እሁድ መጋቢት 9/2010 ዓ. ም. በ17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከአለም 2ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ በ1ኛነት ውድድሩን አጠናቆ ለተመለሰው የልኡካን ቡድናችን የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት አበርክተዋል፡፡

     

በሁለቱም ተቋማት የተበረከተው አጠቃላይ የገንዘብ ሽልማት ወደ 300 ሺህ ብር ገደማ ሲሆን በሥነ ስርአቱ ወቅት የኢፌዲሪ ወ/ስ/ሚ/ር ሚንስትር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በየተራ ባሰሙት የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግር፡- በ17ኛው የአለም የቤት ውስጥ ውድድር ኢትዮጵያን ከአለም 2ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው ይህ ከፍተኛ ውጤት እንድንኩራራ የሚያደርግ ሳይሆን እንደሃገር አሁንም ተፎካካሪዎቻችንን በከፍተኛ  ሁኔታ በልጠን ለመገኘት ጠንክረን መስራት እንዳለብ ያመላከተ ነው፤ በማለት አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም የቡድኑ መሪ ዶ/ር በዛብህ ወልዴ በሰጡት አስተያየት በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለልኡካን ቡድኑ ላደረገው አቀባበል፣ የትራንስፖርት አቅርቦትና ልዩ መስተንግዶ ምስጋናቸው ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

                                                                                                            

በተያያዘ ዜና ቅዳሜ መጋቢት 8/2010 ዓ. ም. በአልጀሪያ – ክሌፍ ከተማ በተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከእስከዛሬዎቹ የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በላቀ ሁኔታ 2 ወርቅ፣ 4 ብር፣ 2 ነሃስና 5 ዋንጫ በማግኘት ከአፍሪካ 2ኛ ሆና በከፍተኛ ውጤት ውድድሯን አጠናቅቃለች፡፡ ቡድኑም በሁለት ምድብ ወደ ሃገሩ በመመለስ ላይ ነው፡፡ የመጀመሪው ምድብ እሁድ ለሊት አዲስ አበባ ገብቷል፤ ሁለተኛው ቡድንም ሰኞ ለሊት አዲስ አበባ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡

ስለሺ ብሥራት፣

የኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ፤

Similar Posts
Latest Posts from