የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ5ኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና እና በ23ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሰለፉ የአትሌቲክስ ልኡካን ቡድን አባላትን ዛሬ ሰኞ መጋቢት 3/2010 ዓ. ም. ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ በአራራት ሆቴል ሸኝቷል፡፡

በአሸኛነት ሥነ ስርዓቱ ላይ ከሁለቱም የልኡካን ቡድኖች የተወከሉ ሴትና ወንድ አትሌቶች፣ እንዲሁም አሰልጣኞቻቸው ስለነበራቸው የስልጠናና ዝግጅት ጊዜ አስረድተው በሚጓዙባቸው የውድድር ሜዳዎች ውጤታማ እንደሚሆኑ ቃል ገብተዋል፡፡

በተጨማሪም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ባስተላለፈው መልእክት ከሁሉ በፊት ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች መለያ መሆን የሚገባው ዲሲፕሊን መሆኑንና በቀጣይ ደግሞ ውጤት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የአትሌቲከሱ ስፖርት አሁን ላይ መሰረት እየያዘ የሚገኝ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን በአግባቡ ሊያበረክት እንደሚገባውም ፕሬዝደንቱ አመልክቷል፡፡

ከኃይሌ ንግግር ቀደም ብሎ መልእክት ያስተላለፉት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ በላይነህ ክንዴ አትሌቶቻችን የሚጠበቅባቸው ባለድል መሆን ብቻ እንደሆነና ከድል መልስ ወርቅ፣ ብርና ነሃስ ለሚያስገኙ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተውላቸዋል፡፡ ክቡር ፕሬዝደንቱም ከአቶ በላይነህ ክንዴ በኋላ እሱም ተመሳሳይ ሽልማት በግሉ እንደሚያበረክት ቃል ገብቷል፡፡

ስለሺ ብሥራት – የኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ኤክስፐርት፤

 

Similar Posts
Latest Posts from