ዜና አትሌቲክስ፣ የካቲት 16/2010፣ ያያ ቪሌጅ – ሱሉልታ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከቻይና ህዝ/ዲ/ሪ/አትሌቲክስ አሶሴሽን ጋር በአምስት ዝርዝር የአትሌቲክስ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት አርብ የካቲት 16/2010 ዓ. ም ከቀኑ 9፡00 ሰኣት ላይ ሱሉልታ በሚገኘው ያያ ቪሌጅ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ከ10 የማያንሱ የቻይና አትሌቲክስ ልኡካን የተገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ም/ፕሬዝዳንቱ አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም፣ የሥራ አስፈፃሚና የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡

ከስምምነት አጀንዳዎች መካከል፡-

  1. ቻይና በአጫጭር ርቀቶችና በሜዳ ተግባራት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በመካከለኛና በረጅም ርቀቶች በየጊዜው ልምድ ለመለዋወጥና በአሰልጣኞች አማካይነት ስልጠናዎችን መስጠት፣
  2. ከእውቀት ሽግግር ባለፈ የአትሌቲክስ ስልጠና ለመስጠትና የስልጠናና ውድድር ቁሳቁሶች ድጋፍ ለማድረግ፣
  3. በየአመቱ ለአመራሮች የጋራ የልምድ ልውውጥ መድረክ ለመፍጠርር፣
  4. የኢንፎርሜሽን ቴክኒዮሎጂና የኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በተመለከተ ሥልጠናዎችን ለመስጠት፣ … የሚሉት በዋናነት የሚጠቀሱ የስምምነት አጀንዳዎች ናቸው፡፡

በስምምነቱ መክፈቻ ወቅት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ባደረገው የመክፈቻና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ሃገራችን ከቻይና ጋር ያላት የትብብር ግንኙነት ረጅም እድሜ ያለው ሲሆን ያንን የቆየ ግንኙነት በአትሌቲክሱ ዘርፍም ይበልጥ አጠናክሮ አንዳችን ከሌላቸኛችን ትምህርትና ተሞክሮ በመቅሰም አትሌቲክስን ለሰላማዊ መስተጋብር መፍጠሪያ መንገድ በማድረግ ለመጠቀም በማሰብ እንደሆነ አስረድቷል፡፡

የቻይናው ተወካይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጣም በርካታ የአትሌቲክስ ሃብት ያላት ሃገር በመሆኗ ቻይናውን ከኢትዮጵያ ጋር በዚህ መንገድ ስምምነት መፈጸማችን ተጠቃሚ ያደርገናል ብለው እንደሚያምኑና ኢትዮጵያም ከቻይና አትሌቲክስ ልታገኘው የምትችለው በጣም በርካታ ጠቀሜታ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ፕሮግራም ከያዛቸው አጀንዳዎች መካከል አዲስ ተሸሽሎ የተገነባውን የፌዴሬሽኑን ድረ-ገጽ (www.eaf.org.et ) ማስተዋወቅ አንዱ በመሆኑ በስፍራው ለተገኙ የስፖርቱ ቤተሰቦችና ለስፖርት ሚዲያ አካላት አስተዋውቋል፡፡

በመጨረሻም የስጦታ ልውውጥ ከተደረገና የፎቶግራፍ ሥነ ስርዓት ከተካሄደ በኋላ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

Similar Posts
Latest Posts from