በ42ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የወከለውና በ4 ወርቅ፣ 4 ብር፣ 1 ነሃስና በድምሩ 9 ሜዳልያዎችን በማግኘት ኢትዮጵያን ከአለምም ከአፍሪካም 2ኛ አድርጎ የተመለሰው ቡድናችን ዛሬ ሰኞ መጋቢት 18/2009 ዓ. ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርስ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
በአቀባበሉ ላይ፡-
የኢፌዲሪ ወ/ስ/ሚ/ር የስፖርት ዘርፍ ሚ/ር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ም/ፕሬዝዳንቱ አትሌት ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም፣ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮ/አባላት፣
የኢትዮጵያ ወ/ስ/አካዳሚ ም/ዳይሬክተር አቶ ወ/ገብርኤል መዝገቡ፣
ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎችና ከተለያዩ የስፖርት ሚዲያዎች ተጋብዘው የተገኙ ባለሙያዎችና የፌዴሬሽኑ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡
በዚህ አቀባበል ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የእንኳን ደህና መጣችሁና እንኳን ደስ ያላችሁ ንግግር ያደረገ ሲሆን ቡድኑ አዲሱን አመራርም ሆነ መላውን የሃገራችንን የአትሌቲክስ ስፖርት ቤተሰብ ያስደሰተ ውጤት ይዞ በመምጣቱ ሊመሰገን እንደሚገባው ገልጾ፣ በተለይ በዚህ ሻምፒዮና ቡድኑ በከፍተኛ ሁኔታ ካሳካቸው ተልእኮዎች መካከል የቡድን መንፈስ መጠበቅ የሚለውን እንደ አመራር ሁሉም የረካበት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይሄም ድል ከአመት በኋከላ እናሳካዋለን ተብሎ ሲጠበቅ ቢቆይም ከአንድ አመት ቀድሞ መታየቱ ትልቅ ድል ነው ብሏል፡፡
የኢፌዲሪ ወ/ስ/ሚ/ር የስፖርት ዘርፍ ሚ/ር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ስንሸኛችሁ እንደተባባልነው ሆናችሁ በመገኘታችሁ ደስ ብሎናል ብለዋል፡፡
ከእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግሮች በኋላ የአበባ አሰጣጥና የፎቶ ግራፍ ሥነ ስርዓትም ተካሂዶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡


Website by REMHAI ICT Solutions and Consulting