ወቅታዊ ዜና፡-

ሰሞኑን በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኮንፌዴሬሽን ኦፍ አፍሪካን ፉት ቦል /CAF/ አመታዊ ጉባዔ ላይ ለመገኘትና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን የአትሌቲክስ ልማት በመጎብኘት ልምድ ለመቅሰም በትናንትናው እለት ምሽት አዲስ አበባ የገቡትን የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን /CAA/ ፕሬዝዳንትና የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር /IAAF/ ም/ፕሬዝዳንት የሆኑትን ሚስተር ካልካባ ማልቡምንና የናይጄሪያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሚስተር ኦግባ ሶሎሞን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴና የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ትላንት መጋቢት 5/2009 ዓ. ም. ምሽት ላይ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ለሁለቱ እንግዶች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን /CAA/ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር የረጅም ጊዜ ጥብቅ የሥራ ቁርኝትና አበረታች የርስ በርስ ግንኙነት ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ የኮንፌዴሬሽኑ ካውንስል አባል ሆና እያገለገለች መሆኗም ይታወቃል፡፡

የናይጄሪያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ያለውንና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ተጠናክሮ የተጀመረውን የአትሌቲክስ ዴቬሎፕመንት ሥራ በማየት ለናይጄሪያ አትሌቲክስ የሚጠቅም ልምድ ለመቅሰም ፕሬዝዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውም በኢትዮጵያ የአትሌቲክሱ ስፖርት ለሌሎች ሃገራትም ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው፡፡

 

 


Website by REMHAI ICT Solutions and Consulting