የ44ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና


ሕግና ደንብ


ሙሉ ዶኩመንቱን ዳውንሎድ ያርጉት (PDF 696KB)


ዓላማ፡ -
1.    በክልሎች፣ በከተማ አስተዳድሮች፣ በክለቦችና በማሠልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር፤
2.    ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት፤
3.    ለብሔራዊ አትሌቲክስ ስልጠና አትሌቶችን ለመምረጥ፤
4.    ከነሐሴ 28/2007 ዓ.ም. እስከ መስከረም 8/2008 ዓ.ም. ድረስ ብራዛቢል (ኮንጎ) በሚካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች ለመምረጥ፤

አንቀጽ አንድ
አጠቃላይ የውድድሩ ደንብ

1.    የውድድሩ መጠሪያ፡- ይህ ውድድር 44ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተብሎ ይጠራል፡፡
2.    ውድድሩ የሚመራው፡- በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በIAAF ውድድር ህግና ደንብ መሠረት ይመራል፡፡
3.    ውድድሩን በበላይነት የሚመራ አካል፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው፡፡
4.    የውድድሩ አግባብነት፡- በአንድ የውድድር ተግባር ሁለት ቡድኖች፣ ሦስት እና ከሦስት በላይ አትሌቶች ተመዝግበው ለውድድር ከቀረቡ ውድድሩ ይካሄዳል፡፡ ከዚህ በታች ከሆነ ግን ውድድሩ አይካሄድም፤ ነገር ግን ያለበቂ ምክንያት ለውድድር ተመዝግቦ ውድድሩን የሰረዘ ቡድን ብር 500.00 (አምስት መቶ ብር) ይቀጣል፤ ብሩን ካልከፈለ ቡድኑ በቀሪዎቹ ውድድሮች ላይ አይሳተፍም፡፡
-    ውድድሩ በክልል፣ በከተማ አስተዳደርና በክለብ የተከፈለ ሳይሆን በአንድነት ሆኖ ቡድኖች በሚያስመዘግቡት ውጤት መሠረት ለአሸናፊዎች ነጥብና የዋንጫ ሽልማት ይሰጣል፡፡

አንቀጽ ሁለት
የውድድሩ ቀንና ቦታ

44ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሰኔ 3-7/2ዐዐ7 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታድየም ይካሄዳል፡፡

አንቀጽ ሦስት
የውድድሩ ዕድሜ

1.    ታዳጊ አትሌቶች ማለትም ዕድሜያቸው 16 ወይም 17 ዓመት የሆኑ አትሌቶች /1990-1991/ ወይም እ.ኤ.አ. /1998-1999/ የተወለዱ በውርወራ ተግባራት (በወንዶች)፣ በ10,000 ሜትር እና በርምጃ ውድድር መሳተፍ አይችሉም፡፡ ነገር ግን በሌሎች የውድድር ተግባራት መሳተፍ ይችላሉ፡፡
አንቀጽ አራት
በውድድር መሳተፍ

አንድ አትሌት በሦስት የግል እና በአንድ የቡድን (ሪሌ) ብቻ መሳተፍ ይችላል፡፡

አንቀጽ አምስት
የምዝገባ ጊዜ

1.    የምዝገባ ጊዜ ከግንቦት 10-22/2007 ነው፡፡ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦችና ተቋማት የተሳታፊዎች ስም ዝርዝርና ሌሎች መረጃዎች ከዚህ ደብዳቤ ጋር ተያይዞ በቀረበው ቅጽ መሠረት ሞልተው መላክ አለባቸው፡፡
2.    ከላይ በተጠቀሰው የምዝገባ ጊዜ ገደብ ውስጥ ያልተመዘገበ ቡድን ብር 3ዐዐ (ሶስት መቶ ብር) በመክፈል ግንቦት 24/2ዐዐ7 ዓ.ም እስከ ቀኑ 11፡00 ብቻ መመዝገብ ይችላል፡፡
3.    ማንኛውም ተሳታፊ ቡድን በየውድድር ተግባሩ ሚኒማውን የሚያሟሉ አራት አትሌቶችን ማስመዝገብ ይችላል፡፡
4.    ለዱላ ቅብብል እያንዳንዱ ቡድን ከአራት እስከ ስድስት አትሌቶች ማስመዝገብ ይችላል፡፡

አንቀጽ ስድስት
የውድድሩ ዓይነትና ሚኒማ

1.    ሚኒማው በ2007 ዓ.ም. በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተደረጉት ውድድሮች የተመዘገቡ መሆን አለባቸው፤
2.    ማንኛውም ክልል/ክለብ አትሌቱ ሚኒማ ያስመዘገበበትን የሻምፒዮና ስም፣ ከተማና ቀን ውድድሩን ጨምሮ መገለጽ ይኖርበታል፡፡
3.    ለ44ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የውድድር ዓይነቶችና የመግቢያ ሚኒማ፡-


አንቀጽ ሰባት
የተወዳዳሪ ቅያሪ

1.    ማንኛውም ቡድን በየውድድር ተግባሩ በየቀኑ የተወዳዳሪ ለውጥ ማድረግ ከፈለገ ቀጣይ ውድድር ከመደረጉ ከአንድ ቀን በፊት (eve of each event) እስከ ቀኑ 6፡00 ሰዓት ለውድድሩ ከተመዘገቡት አትሌቶች ውስጥ ለቅያሪ በተዘጋጀው መቀየሪያ ቅጽ አትሌቶችን በማስመዝገብ የውድድሩ ቴክኒካል መረጃ ክፍል (TIC) ማቅረብ አለበት፡፡ የተወዳዳሪዎች ቅያሪ የሚደረገው በየውድድር ተግባራቱ ከተመዘገቡት አራት አትሌቶች ብቻ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከተጠቀሰው ሰዓት ውጭ ለሚቀርበው የተወዳዳሪዎች ቅያሪ ጥያቄ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
2.    በዱላ ቅብብል የተወዳዳሪዎች ጥንቅርና የአሯሯጥ ቅደም ተከተል ምዝገባ የሚካሄደው ለዱላ ቅብብል ውድድር የስም ጥሪ ከመደረጉ ከአንድ ሰዓት በፊት ለቴክኒካል መረጃ ክፍል ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡
3.    ለዱላ ቅብብል ከተመዘገቡት ከማንኛውም የውድድር ተግባራት ቀይሮ ማወዳደር ይቻላል፡፡ ይኸውም ለመጀመሪያ ዙር ውድድር ብቻ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በቀጣይ ዙር ውድድሮች መቀየር የሚቻለው ከተመዘገቡት አትሌቶች ብቻ ሆኖ ሁለት አትሌት መቀየር ይቻላል፡፡

አንቀጽ ስምንት
የአትሌቱ ጤንነት

በውድድሩ ተካፋይ የሚሆን አትሌት ጤናው የተሟላ መሆን አለበት፤ ጤናው ያልተሟላ አትሌት በውድድሩ ተሳትፎ ቢገኝና ጉዳት ቢደርስበት ተጠያቂ የሚሆነው ክልሉ/ከተማ አስተዳድሩ፣ ክለቡ እና አትሌቱ ይሆናል፡፡
አንቀጽ ዘጠኝ
ውጤትን ስለመግለጽ

1.    የዕለቱ ውድድር ውጤቶች ለተወዳዳሪዎችና ለቡድኖች በየውድድሩ ጣልቃ በአስተዋዋቂ፣ በኮሙኒኬና በቻርት ይገለፃል፡፡
2.    በተገለጹት ውጤቶች ላይ ስህተቶች ካሉ ወዲያውኑ የቡድን መሪው/አሠልጣኝ የውድድሩ ቴክኒካል መረጃ ክፍል (TIC) በመቅረብ የማስተካከያ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል፡፡
3.    ከውድድሩ ቴክኒካል መረጃ ክፍል (TIC) የውድድሩ ውጤት ይፋ ሳይደረግ ውጤቱን ለህዝብ መግለጽ የተከለከለ ነው፡፡

አንቀጽ አስር
ክስና ይግባኝ ስለማቅረብ

1.    የአትሌት ተገቢነት የክስ ጥያቄ ማቅረብ የሚቻለው ውድድሩ ከመጀመሩ ከ30 ደቂቃ በፊት ነው፡፡
2.    የውድድር ውጤቶችን ወይም የውድድር ተግባር ሁኔታን በተመለከተ የክስ ጥያቄ የሚቀርበው ውጤቱ ይፋ በሆነ በ30 ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
3.    ማንኛውም የክስ ጥያቄ መጀመሪያ የሚቀርበው ለውድድሩ ዳኛ (refree) በቃል በአትሌቱ፣ በአሠልጣኙ ወይም በቡድን መሪው አማካይነት ሊሆን ይችላል፡፡ የውድድር ዳኛው ውሳኔ መስጠት ወይም ጉዳዩን ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሊያቀርብ ይችላል፡፡
4.    በዳኛው ውሳኔ ያልተስማማ አካል በጽሑፍ ከብር 300.00 (ሦስት መቶ ብር) ጋር ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ዳኛው ውሳኔ በሰጠ በ30 ደቂቃ ውስጥ ክስ ማቅረብ ይችላል፡፡
5.    ክሱ በክስ ሰሚ ኮሚቴ ተጣርቶ ተገቢ ክስ ሆኖ ከተገኘ የተያዘው ብር ተመላሽ ሆኖ ክሱ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ክሱ ተቀባይነት ካላገኘ የተያዘው ብር ለፌዴሬሽኑ ገቢ ሆኖ ውሳኔው የፀና ይሆናል፡፡

አንቀጽ አስራ አንድ
በውድድርና በሽልማት ጊዜ አለባበስ

1.    ማንኛውም ተወዳዳሪ የክልሉን፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ የክለቡና የማሠልጠኛ ማዕከሉን መለያ የሆነውን የስፖርት ትጥቅ መልበስ አለበት፤ መለያ ለብሶ ያልቀረበ ተወዳዳሪ መወዳደር አይችልም፤ ተወዳድሮ ቢገኝ ውጤቱ ይሰረዛል፡፡
2.    ማንኛውም የሜዳሊያ ተሸላሚ አትሌት የክልሉን፣ ከተማ መስተዳደሩን፣ የክለቡን ወይም የተቋሙን መለያ የሆነውን የስፖርት ልብስ ለብሶ መቅረብ አለበት፡፡
አንቀጽ አስራ ሁለት
የመወዳደሪያ መሮጫ ቁጥር
 
ማንኛውም ተወዳዳሪ አትሌት የመወዳደሪያ ቁጥር ሊኖረው ይገባል፣ ቁጥሩ የሚለጠፈው ግልጽ ሆኖ በሚታይ ቦታ በደረትና በጀርባ ላይ ነው፡፡ የምርኩዝ ዝላይና የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪዎች አንድ የመወዳደሪያ ቁጥር ብቻ በደረት ወይም ከጀርባ ላይ ለጥፎ መወዳደር ይቻላል፡፡ በሪሌ ውድድር ከጀርባ ቁጥር በተጨማሪ አትሌቱ የክልሉን፣ ከተማ አስተዳደሩን ወይም ክለቡን ስም የሚገልጽ ጽሑፍ በደረቱ ላይ መለጠፍ አለበት፡፡ የመወዳደደሪያ ቁጥር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቴክኒካል ስብሰባ ቀን ይሰጣል፡፡

አንቀጽ አስራ ሦስት
በስም ጥሪ ቦታ በሰዓት መገኘት

ማንኛውም ተወዳዳሪ ውድድሩ ከመጀመሩ ቢያንስ ከ45 ደቂቃ በፊት በስም ጥሪ ቦታ በመገኘት ለውድድሩ ዝግጁ መሆኑን ለስም ጠሪ ዳኞች ማሳወቅ ይኖርበታል፤ በስም ጥሪ ቦታ ተገኝቶ ስሙን ለስም ጠሪ ዳኞች ያላሳወቀ አትሌት በውድድሩ ላይ መካፈል አይችልም፤ ተወዳድሮ ቢገኝ ውጤቱ ይሰረዛል፡፡

አንቀጽ አስራ አራት
የተወዳዳሪ ቴሴራ ወይም መታወቂያ

1.    አትሌቶች በስም ጥሪ ቦታ ማንነታቸውን የሚገልጽ በዘመኑ በክልሉ/ከተማ አስተዳደሩ የታደሰ ቴሴራ ይዘው መቅረብ አለባቸው፤ ስርዝ ድልዝ ያለው ቴሴራ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ቴሴራ የሌለው በውድድሩ ላይ መሳተፍ አይችልም፤
2.    በቴሴራው/መታወቂያው ላይ የትውልድ ዘመን መገለጽ አለበት፤
3.    በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን በመወከል ወይም በግሉ በውጭ ውድድር የተካፈለ አትሌት ፓስፖርት ማቅረብ አለበት ወይም የውጭ ውድድር ዕድል ባያገኝም ፓስፖርት ያለው አትሌት ፓስፖርቱን ማቅረብ አለበት፡፡

አንቀጽ አስራ አምስት
ሽልማት

1.    በእያንዳንዱ የውድድር ተግባር ከ1ኛ-3ኛ ለሚወጡ አትሌቶች በሁለቱም ፆታ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ሽልማት ይሰጣል፤
2.    በውድድሩ በቡድን ነጥብ የወንድ አሸናፊ እና የሴት አሸናፊ ለየብቻቸው የዋንጫ ሽልማት ይሰጣል፤
3.    የሴትና የወንድ ነጥብ ተደምሮ አብላጫ ነጥብ ላስመዘገበ አጠቃላይ ቡድን የዋንጫ ሽልማት ይሰጣል፤
4.    በውድድሩ ሦስት ወርቅ እና ከዚያ በላይ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች ልዩ ሽልማት ይሰጣል፡፡አንቀጽ አስራ ስድስት
ያልተገባ ፀባይ

ማንኛውም ተወዳዳሪ አትሌት፣ አሰልጣኝ፣ የቡድን መሪ፣ ወጌሻ ወይም ሌሎች የቡድን አባላት ውድድሩ በሚከናወንበት ወቅት ያልተገባ ፀባይ ካሣየና ውድድሩን በሚመሩ ዳኞች ወይም የውድድር አዘጋጆች ሪፖርት ቀርቦ ጥፋቱ ከተረጋገጠ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተዘጋጀው የአሠልጣኞች፣ አትሌቶችና የክለቦች የሥነ-ምግባር ደንብ አንቀጽ አስር መሠረት ይቀጣል፡፡ 

አንቀጽ አስራ ሰባት
በውድድሩ መክፈቻና መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘት

1.    በውድድሩ ተካፋይ የሚሆኑ ቡድኖች የቡድናቸውን አርማ ይዘው በተሟላ ስፖርታዊ አለባበስ እንዲሁም ባህላዊ አልባሳትን ለብሰው በውድድሩ መክፈቻና መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘት አለባቸው፤
2.    እንደአስፈላጊነቱ ከውድድር በኋላ በሚደረጉ ቴክኒካል ስብሰባዎች የቡድን መሪዎች/አሠልጣኞች መገኘት አለባቸው፡፡

አንቀጽ አስራ ስምንት
የቴክኒካል ስብሰባ

የቴክኒካል ስብሰባ ሰኔ 02/2ዐዐ7 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡ዐዐ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡ በስብሰባው ከየቡድኑ አንድ ቡድን መሪና አንድ አሠልጣኝ ብቻ ይሳተፋሉ፡፡

አንቀጽ አስራ ዘጠኝ
የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቡድን ኮታ

1.    የትግራይ ክልል 45 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
2.    አማራ ክልል 45 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
3.    ኦሮሚያ ክልል 45 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
4.    ደቡብ ክልል 45 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
5.    አዲስ አበባ አስተዳደር 45 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
6.    ሐረሪ ክልል 20 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
7.    ድሬዳዋ አስተዳደር 20 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
8.    ጋምቤላ ክልል 15 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
9.    አፋር ክልል 15 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
10.    ሱማሌ ክልል 15 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
11.    ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 25 ሰው ቡድን መሪና አሰልጣኝን ጨምሮ፤
ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከተሰጣቸው ኮታ ውጪ በራሳቸው ወጪ ተጨማሪ አትሌቶችን በውድድሩ ማሳተፍ የሚችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡


Website by REMHAI ICT Solutions and Consulting