የአትሌቲክስ ስፖርት በኢትዮጵያ መቼ፣ የትና እንዴት እንደተጀመረ የሚገልፁ ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት ባይቻልም ከ1890 ዓ. ም. ቀደም ብሎ በትምህርት ቤቶችና በወታደራዊ ካምፖች ይዘወተር እንደነበር ግን ይነገራል፡፡

ቀስ በቀስም አትሌቲክስ በሃገራችን አብዛኛው ሥፍራ እየተለመደና በህዝቡም ዘንድ እየተዘወተረ ስለመጣ ስፖርቱን በበላይነት ሊመራ የሚችል ተቋም ‹‹ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን›› በሚል መጠሪያ በ1941 ዓ. ም. ተቋቋመ፡፡

የተቋቋመበት አጠቃላይ ዓላማ፡-

በአለም አቀፉ የስፖርት ህግ መሠረት በአንድ ሀገር በአንድ የስፖርት ዓይነት ሊኖር የሚችለው አንድ ሀገር አቀፍ ፌዴሬሽን ብቻ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ የሀገሪቱን ሕግና ደንብ ጠብቆ በሕዝብ፣ በመንግስትና በድርጅቶች ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ሀገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተግባራትን የሚያከናውንና ከአጠቃላይ የህብረተሰቡ አትሌቲክስ ስፖርት እንቅስቃሴ በመነሳት በተለይ የወጣቱን ትውልድ ግንዛቤና ተሳትፎ በማጠናከር የላቀ ችሎታ ያላቸው ምርጥ ስፖርተኞች እንዲፈሩ በማድረግ በአለም አቀፍ ደረጃ የአገራችንን ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነት ማስፋት በሚል አጠቃላይ ዓላማ የተቋቋመ ማህበር ነው፡፡

ተግባራቱም፡-

1.      የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን በወጣው ማቋቋሚያ መመሪያ እንዲሁም በአለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ሕገ ደንብ መሠረት በሀገሪቱ ውስጥ የአትሌቲክስ ስፖርትን በበላይነት ይመራል፣ ስለሚስፋፋበት ሁኔታ ስልቶችን ይቀይሳል፤

2.     የአትሌቲክስ ስፖርቱን በሚመለከት የመንግስት ፖሊሲን፣ ሕግን፣ ደንብንና መመሪያዎችን ይፈፅማል፣ ያስፈፅማል፤

3.     ደረጃቸውን የጠበቁ የአትሌቲክስ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲቋቋሙ ይደግፋል ዕውቅና ይሰጣል፤

4.     የአትሌቲክስ ስፖርትን የሚመለከቱና ተዛማጅ መረጃዎችን ያሰባስባል፣ ያደራጃል፣ ያሰራጫል፤

5.     በሀገር ውስጥ ከአንድ ክልል በላይ በሚያሳትፍ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ሀገር በላይ የሚደረጉ የአትሌቲክስ ውድድሮችን ያካሂዳል፣ ፈቃድ ይሰጣል፤

6.     የአትሌቲክስ ስፖርት ክለቦች ስለሚደራጁበት ሁኔታ መመሪያ ያወጣል፣ ተፈፃሚነቱን ይከታተላል፤

7.     የታዳጊ፣ የወጣቶችና የሴቶች ተሳትፎ ስለሚያድግበት ሁኔታ ስልት ይቀይሳል፤

8.     ምርጥ አትሌቶች እንዲፈሩና ዘመናዊ ስልጠና እንዲያገኙ ስልት ይቀይሳል፤

9.     ከአለም አቀፍና ከሀገር ውስጥ የአትሌቲክስ ተቋማት ጋር በመተባበር ኮርሶችን፣ ሴሚናሮችን፣ ወርክሾፖችንና ስልጠናዎችን ያዘጋጃል፣ ዕውቅና ይሰጣል፤

10.     የአትሌቲክስ ስፖርቱን በሚመለከት በአህጉራዊና አለም አቀፋዊ ውድድሮችና ስብሰባዎች ላይ ይሳተፋል፣ የተላለፉ ውሳኔዎችንም ተግባራዊ ያደርጋል፤

11.       የአሰልጣኞችንና የዳኞችን የመመልመያ መስፈርት ያዘጋጃል ደረጃ ያወጣል ፈቃድ ይሰጣል፤

12.      አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ የአትሌቲክስ ስፖርት እንዲስፋፋ ድጋፍ ያደርጋል፤

13.      የአትሌቲክስ ሰፖርትን ለማሳደግ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ይሳተፋል፤ የገቢ ማስገኛ ተቋማትንም ያቋቁማል፤

14.     የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ይሰራል፤

15.      ለኮሚሽን መ/ቤቱ በየጊዜው (በየሩብ ዓመቱ) የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀርባል፤

16.     የውስጥ መተዳደሪያ ደንብና መመሪያዎች በማውጣትና በጠቅላላ ጉባኤ በማስፀደቅ፣ በሥራ ላይ ያውላል፤

17.      ኢትዮጵያ የተቀበለችውን የፀረ-ዶፒንግ ኮንቬንሽን ያከብራል ያስከብራል፤

18.     በክልሎች ፌዴሬሽኖች እንዲደራጁ ድጋፍ ያደርጋል፣ እውቅና ይሰጣል፣ ለተፈፃሚነቱ መመሪያ ያወጣል፤

19.     በአትሌቲክስ ስፖርት ዙሪያ የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ሰዎችና አካላት በተለያዩ መንገዶች ዕውቅና ይሰጣል፤

20.    በአትሌቲክስ ስፖርት ዙሪያ ለሚነሱ አለመግባባቶችና ክርክሮች ዳኝነት ይሰጣል፤

21.      በአመት አንድ ጊዜ የፌዴሬሽኑን የጠቅላላ ጉባኤ ያካሂዳል፤

22.     ከስፖርት ጋር በተያያዙ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ይሳተፋል፡፡

23.     ውል ይዋዋላል፣ ይከሳል፣ ይከሰሳል፡፡

ፌዴሬሽኑ በተቋቋመበት ወቅት የነበረውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ኮሎኔል ጌታሁን ተክለማርያም በበላይነት ይመሩና ያገለግሉ እንደነበር፣ ከእኝህ ሰው በኋላ ደግሞ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው ተተክተው የአትሌቲክስ ስፖርቱን ይመሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ የተለያዩ አማተር አገልጋዮች ፌዴሬሽኑን በበጎ ፈቃደኝነት በመምራት አሁን ያለበት ደረጃ ያደረሱት ሲሆን አቶ ሙሉጌታ ኃይለማርያምን ተክተው ክብርት ወ/ሮ ብሥራት ጋሻውጠና ከ1994 ዓ. ም. በኋላ እስከ 2004 ዓ. ም. ማብቂያ ድረስ  ያገለገሉ ብቸኛዋ ሴት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ነበሩ፤ እርሳቸውን ተክተው እስከ አሁን በመምራት ላይ የሚገኙት ደግሞ የተከበሩ አቶ አለባቸው ንጉሴ ናቸው፡፡

ከአህጉርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አኳያም  ፌዴሬሽኑ፡- ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር፣ ከአዲዳስ ኩባንያ፣ ከአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን፣ ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅንና ከአቻ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ጋር መልካም የሚባልና በአርዓያነት ሊጠቀስ የሚችል ግንኙነት ያደርጋል፡፡

ቀደም ሲል በተጠቀሰው ዓመትም ፌዴሬሽኑ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) አባል በመሆን ሲመዘገብ፣ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን (CAA) እና በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን (EAAR) ውስጥ ከካውንስል አባልነት ባለፈ በአመራርነት እንድታገለግል ስለተመረጠች ስፖርቱ በአፍሪካ ደረጃም እንዲስፋፋ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጓን ቀጠለች፡፡ 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከምሥረታው በኋላ ስፖርቱን በማሳደግና ክለቦችን በማቋቋም የተለያዩ ውድድሮችን ማካሄድ በመጀመሩ በ1958 ዓ. ም. ‹‹የሸዋ ጠቅላይ ግዛት አትሌቲክስ ሻምፒዮና›› በሚል የመጀመሪያውን አገር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር  በወታደራዊ ካምፖች፣ በት/ቤቶችና በአንዳንድ ቡድኖች መካከል ማከናወን ቻለ፡፡

እየዋለ እያደረም የአትሌቲክስ ስፖርት በሃገሪቱ እያደገ በመምጣቱና በኣለም አቀፍ ውድድሮች ተሣታፊ ሊሆኑ የሚችሉ አትሌቶች መጥቀው መውጣት በመቻላቸው እ.ኤ.አ. በ1956 ዓ. ም. በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ በተደረገው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአትሌት ባሻዬ ፈለቀ፣ በአትሌት ገብሬ ስንቄ፣ በአትሌት ዋሚ ቢራቱ እና በሌሎችም አትሌቶች አማካይነት ተካፍላለች፡፡ ቀጥሎም እ.ኤ.አ. በ1960 ዓ. ም. በኢጣልያ ሮም ከተማ በተካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች አገራችን በማራቶን ሩጫ ተሳትፋ በአትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ አሸናፊ በመሆን ለአፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የወርቅ ሜዳልያና ክብር በማስመዝገብ በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ በቀዳሚነት ለመቀመጥ ቻለች፡፡   

በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በአትሌቲክሱ ስፖርት በተለይም በረጅም ርቀት ሩጫ አሸናፊነት እየታወቀች የመጣችው ኢትዮጵያ ከ4 ዓመት በኋላ በጃፓን ቶኪዮ በተደረገው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የማራቶን ውድድር በፈር ቀዳጁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ አማካይነት ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ልትደግም ችላለች፡፡

በአፍሪካም ሆነ በሃገራችን ከእነዚህ ፋና ወጊ ከሆኑት የአትሌቲክስ ድሎች በኋላ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ተተኪ አትሌቶች በዓለም የኦሎምፒክ ጨዋታዎች፣ በዓለም ሃገር አቋራጭ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችና በሌሎችም ውድድሮች ላይ በመሳተፍ የአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል፡፡ እነ አትሌት ማሞ ወልዴ፣ ሽብሩ ረጋሳ፣ ቶለሳ ቆቱ፣ እሸቱ ቱራ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ መሐመድ ከድር፣ ደራርቱ ቱሉ፣ በላይነህ ዲንሳሞ፣ ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣…. ከብዙዎቹ ባለድሎቻችን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡  

በዚህም መሰረት ላለፉት 60ዎቹ አመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየአመቱ በሚያካሂዳቸው ከ10 በላይ የሃገር ውስጥ ውድድሮች ላይ የመላ ሃገሪቱ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡  

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለዘመናት ተከብሮ የቆየውንና በጀግኖች አትሌቶቻችን የሁልጊዜም ድል ያሸበረቀውን የአትሌቲክስ ስፖርት ክብሩ ተጠብቆ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ተግቶ በመስራት በአሁኑ ወቅት በአመት ከ15 የማያንሱ የአገር ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮችን የዓለም አቀፉን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የውድድር ካላንደር መሰረት እያደረገ በማካሄድ በርካታ ተተኪና ወጣት አትሌቶችን ማፍራት ችሏል፡፡

በታሪካችን ውስጥ ያየናቸው በርካታ ስመ ጥር አትሌቶች ቢኖሩንም ከበርካቶች መካከል ለዋቢነት፤

ከፈር ቀዳጆቹ መካከል፡- አትሌት ባሻዬ ፈለቀ፣ ገብሬ ስንቄ፣ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ሽብሩ ረጋሳ፣ ቶለሳ ቆቱ፣ እሸቱ ቱራ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ መሐመድ ከድር፣ ዮሐንስ መሃመድና የመሳሰሉት፤

ከተከታዮቹ- ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ በላይነህ ዲንሳሞ፣ ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ቁጥሬ ዱለቻ፣ የመሳሰሉት፤

ከቅርቡ ዘመን፡- ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣ ስለሺ ስህን፣ ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም የመሳሰሉት፤

ከአሁኖቹ ደግሞ፡- መሃመድ አማን፣ አልማዝ አያና፣ ሙክታር እንድሪስ፣ ህይወት አያሌው፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ አለሚቱ ሃሮዬ፣ ሃጎስ ገ/ህይወት፣ ሶፍያ አሰፋ፣ የማነ ፀጋዬ፣ ቡዜ ድሪባ፣ መረሣ ካህሳይ፣ ዳዊት ስዩም፣ ያሲን ሃጂ፣ ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ፋንቱ ማጊሶ፣ ሞስነት ገረመው፣ አለሚቱ ሃዊ፣ ጎይተቶም ገ/ስላሴና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

 

 

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

 

ኮሙኒኬሽንና ማርኬቲንግ ዲፓርትመንት

 


Website by REMHAI ICT Solutions and Consulting